ከ208,530 ብር በላይ የሚገመት ሕገወጥ መድኃኒት፣ አደንዛዥ ዕፆችና አልሚ ምግቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡
የኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ከኦሮሚያ ብ/ክ/መ በቦረና ዞን በሞያሌ ወረዳ እና በሱማሌ ብ/ክ/መ ሊበን ዞን ዳዋ ወረዳ ከሁለቱ የክልል ጤና ተቆጣጣሪዎች ጋር በመተባበር በሱቆችና መድኃኒት ቤቶች ላይ በተደረገው ድንገተኛ ፍተሻ ከ181,060 ብር በላይ የሚገመት ሕገወጥ መድኃኒት፣ አደንዛዥ ዕፆችና አልሚ ምግቦች አገልግሎት ላይ ከመዋላቸው በፊት በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ታውቋል፡፡
በቁጥጥር ስር የዋሉት ሕገወጥ መድኃኒት፣ አደንዛዥ ዕፆችና አልሚ ምግቦች በስምንት ሱቆች እና በሦስት መድኃኒት ቤቶች ውስጥ የተገኙ ሲሆን፤ በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ያልተመዘገቡና የቅዝቃዜ ሰንሰለታቸውን ሳይጠብቁ በኮንትሮባንድ መልክ መግባታቸው ተገልጿል፡፡
ባለስልጣኑ ሕገወጥ መድኃኒቶቹንና ምግቦቹን ለአገልግሎት እንዳይቀርቡ በማድረግ ሱቆችና መድኃኒት ቤቶቹ እንዲታሸጉ አድርጓል ፡፡
በተመሳሳይ የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከህብረተሰብ በደረሰ ጥቆማ መሰረት ከፖሊስ አካላት ጋር በመተባበር በድሬዳዋ ከተማ አባይ በሚባል መድኃኒት ቤት ውስጥ እንዲሁም በአንድ ግለሰብ ሲዘዋወሩ የነበሩ ያልተመዘገቡ 27,470 ብር የሚገመቱ መድኃኒቶች በተደረገ ድንገተኛ ፍተሸ የመድኃኒት ቤቱ ባለቤት በፖሊስ በቁጥጥር ስር እንዲውል በማድረግ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድበት መደረጉ ታውቀዋል፡፡
ባላስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 1112/2011 በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት ምርት ተኮር ቁጥጥሩን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት አጠናክሮ እንደሚቀጥል በማስታወቅ ህብረተሰቡ የቁጥጥሩ ባለቤት በመሆን ከማንኛውም ህገወጥ የምግብና የመድኃኒት ንግድና ዝውውር እራሱን በመጠበቅ የቁጥጥር ስራውን እዲያግዝ ተጠይቋል፡፡
በመቀጠልም ህብረተሰቡ መሰል ህገወጥ የምግብና የመድኃኒት ንግድና ዝውውር ድርጊቶች ሲፈጸሙ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በነጻ ስልክ መስመር በ 8482 ወይም በአካባቢው ለሚገኙ የፍትህ አካላትና የጤና ተቆጣጣሪዎች እንዲጠቁም ባለስልጣን መ/ ቤቱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡