የኢትየጵያ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ደረጃቸውን ያልጠበቁና ሐሰተኛ የመድኃኒት ምርቶችን በመለየት ከገበያ ውጪ እንዲሆኑ ለማድረግ እንዲሁም የመድኃኒት ሥርጭትን ለማሳለጥ የሚረዳ የመድኃኒት ክትትል (ባር ኮዲንግ፣ዳታ ማትሪክስና ሌሎች) ሥርዓት ለመዘርጋት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።
የባለሥልጣኑ መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ት ሄራን ገርባ የመድኃኒት ክትትል ሥርዓት አተገባበር (Pharmaceutical product traceability) ረቂቅ መመሪያን ለማዳበር ከባለድርሻ አካላት ጋር የተደረገውን የምክክር አውደጥናት በንግግር ሲከፍቱ እንዳሉት ባለሥልጣኑ መድኃኒት ተመርቶ ጥቅም ላይ እስኪውል ያለውን የመድኃኒት ሥርጭት ሠንሠለት በመቆጣጠር የታካሚዎችን ደህንነት ለማረጋገጥ እንዲሠራ በህግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የመድኃኒት ዝውውርን የሚመለከት የመረጃ ልውውጥን ለማቀላጠፍና አገልግሎቶችን ለማዘመን የሚረዱ የተለያዩ የአሠራር ሥርዓቶችንና የመዘርጋት ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
ከእነኝህም ተግባራት መካከል በሥርጭት ሠንሠለት ውስጥ መድኃኒቶችን ለመለየትና መረጃ ለመለዋወጥ የሚያስችል ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ የመድኃኒት ክትትል ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ አንዱ ነው፡፡
የመድኃኒት ክትትል ሥርዓት አንድ መድኃኒት በሥርጭት ሠንሠለት ውስጥ የሚያደርገውን ዝውውር በተለያዩ መስፈርቶችና ሥርዓቶች በመታገዘ ለመለየትና ለመከታተል የሚያስችል አዲስ አሠራር ነው፡፡
ባለሥልጣኑ ይህንን ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲያከናውን የቆየ ሲሆን ሥርዓቱ የሚመራበት ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቶ ለባለድርሻ አካላት ይፋ ማድረግ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተከታታይ ውይይት ማድረግና ለውይይት የቀረበውን ይህ ረቂቅ መመሪያ ማዘጋጀት ይገኙበታል፡፡
የክትትል ሥርዓቱን ለመተግበር በመድኃኒት ሥርጭት ሠንሠለት ውስጥ ያሉ ተዋናዮች በተለይም የመድኃኒት አምራቾች ፣ አስመጪዎችና ጅምላ አከፋፋዮች ድርሻ ወሳኝ በመሆኑ የምክክር መድረኩ መዘጋጀቱን ዋና ዳይሬክተሯ ገልፀው ለመድረኩ ተሳታፊዎች የመመሪያው አስፈጻሚዎች በመሆናቸው ለአሠራር በሚመችና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲዘጋጅ ለማድረግ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡