የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን በሕገ-ወጥ ምግብና መድኃኒት ንግድና ዝውውር፣ በትምባሆ እና አልኮል ቁጥጥር እና ምግብን ከባእድ ነገር ጋር መቀላቀል ዙሪያ የባለድርሻ አካላት ውይይትና የሕዝብና የሚዲያ ንቅናቄ መድረክ በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች ከመጋቢት 9 /2013 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 10/2013 ዓ.ም. አካሄደ።
ፕሮግራሙ በጥናት በተለዩ የአገራችን አከባቢዎች በደሴ፣ በጅማ፣ በጅግጅጋ፣ በአርባምንጭ እና በአዲስ አበባ ከተማ የባለ ድርሻ አካላት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የፍትህ አካላት፣ የሚዲያ አካላት፣ የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀትና ክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት የህዝብ ንቅናቄዉ ተካሂዷል።
የሕዝብ ንቅናቄው ዋናው ዓላማ በሕገ-ወጥ ምግብና መድኃኒት፣ የህክምና መሳሪያና የውበት መጠበቂያ ንግድና ዝውውር በትምባሆ እና አልኮል ቁጥጥር፣ እና ምግብን ከባእድ ነገር ጋር መቀላቀል ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮችን ቀድሞ በመከላከል የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ሲሆን ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ በየደረጃዉ ያሉ ባለድርሻ አካላት፣ ህብረተሰቡ እና በየአካባቢው የሚገኙ የሚዲያ አካላት የጋራ ግንዛቤ አግኝተው በባለቤትነት ስሜት የበኩላቸዉን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል ነዉ።
በየከተሞቹ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ሕገወጥ የምግብ ንግድና ዝውውር፣ ህገወጥ የጤና ግብአት ንግድና ሀገራዊ ሁኔታ እንዲሁም ትምባሆና አልኮል እያስከተለ ያለውን ጉዳትና በአዋጅ 1112/2011 እና ሌሎች ትንባሆን ለመቆጣጠር የሚቀመጡ ሕጎች አተገባበርና ነባራዊ ሁኔታ በተመለከተ የመወያያ ጽሁፍ ቀርበው ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኃላ ስምምነት ላይ በመድረስ የቀጣይ የጋራ አቅጣጫ ተቀምጧል።
በዚሁ የህዝብ ንቅናቄ ፕሮግራም በየደረጃው ያሉ የወጣት አደረጃጀቶች ሕገወጥ የምግብ፣ የመድኃኒት፣ የህክምና መሳሪያ እና የውበት መጠበቂያ ምርቶች ግድና ዝውውር፣ ምግብን ከባእድ ነገር ጋር መቀላቀል፣ በአልኮልና ትምባሆ ቁጥጥር እንዲሁም ህብረተሰቡ ከኮቪድ ስርጭት ራሱን መከላከል እንዳለበት ግንዛቤ ለመፈጠር የሚያስችሉ ባነሮችን በመያዝ በማርሸ ባንድ እና የወጣቶች የሰርከስ ቡድን በመታጀብ በእግር ጉዞ የህዝብ ንቅናቄ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን በጤና ግብዓት ቁጥጥር ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚያስችሉ የተለያዩ መልዕክቶችን ያያዙ ቢልቦርዶች የሕዝብ ንቅናቄዉ በተከሄደባቸዉ ከተሞች በተመረጡ ዋናዋና ቦታዎች ተከፍተዉ ለእይታ ክፍት ሆነዋል።
በተጨማሪም የህዝብ ንቅናቄ በሚደረግባቸው ቦታዎች ሚዲያውን በማስተባበር ጉዳዩን በአጀንዳነት በመያዝ ህብረተሰቡን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ተሠርቷል።