የጥራት ደረጃቸውን ያላሟሉ መድኃኒቶችና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምግቦች ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ በቁጥጥር ሥር በማዋል እንዲወገዱ ተደረገ፡፡
የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በ2011 በጀት ዓመት በመግቢያና መውጫ ኬላዎች ባደረገው ቁጥጥር ደህንነታቸውና ጥራታቸውን ያልጠበቁ የምግብና የመድኃኒት ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ በቁጥጥር ሥር በማዋል እንዲወገዱ ማድረጉን አስታወቀ።
ጥራትና ደህንነታቸው ሳይጠበቅ በሕገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ምርቶች በጥቂቱ
በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በመግቢያና መውጫ ኬላዎች በተደረገው ቁጥጥር 4718.77 ቶን የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው፣ በጉዞ ወቅት የተበላሹና የአምራች ድርጅታቸው ስም የማይታወቁ የምግብ ጥሬ ዕቃ፣ ሩዝ፣ አኩሪ አተርና ዘይት እንዲሁም 44.85 ሜ.ቶን የተበላሸ ስኳር የጥራትና ደህንነት መጓደል ያለባቸው የምግብ ምርቶችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በማገድ የማጣራት ሥራ በመሥራት እንዲወገድ መደረጉን ገልጿል፡፡
የፈዋሽነት፣ የደህንንትና የጥራት ደረጃቸውን የማያሟሉ 31.16 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ መድኃኒቶች፣ የህክምና መሳሪያዎችና የመዋቢያ ምርቶች በመግቢያና መውጫ ኬላዎች እንዲሁም በኦዲቲንግ ኢንስፔክሽን ወቅት በቁጥጥር ሥር በማዋል እንዲወገዱ መደረጋቸውን ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ገልጿል፡፡
በማያያዝም በበጀት ዓመቱ ባለስልጣን መ/ቤቱ በተለያዩ ድርጅቶች ተመርተው ወደ ገበያ በተሰራጩ ምርቶች ላይ በተደረገው የገበያ ቅኝትና የድህረ ገበያ ናሙና ፍተሻ እንዲሁም ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሠረት የመጠቀሚያ የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው ምረቶችን፤ በብሔራዊ ደረጃ የተቀመጠውን መስፍረት ያላሟሉ፤ ምንም ዓይነት ገላጭ ጽሁፍ የሌላቸው፤ የአምራች አድራሻ እና መለያ ቁጥር የሌላቸው የተለያዩ የዘይት፣ የወተት ተዋጽዖ፣ ከረሜላ፣ ማስቲካ እና ብስኩት ምርቶች ላይ ባለስልጣኑ የአስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱ የሚታወስ ነው፡፡
በቀጣይም በ2012 በጀት ዓመት ባለስልጣኑ በአዋጅ ቁጥር 1112/2011 በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሠረት ምርት ተኮር ቁጥጥሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡