የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አዲሱን የተቋሙን ብራንድ በይፋ አስመረቀ፡፡
ግንቦት 30 2014 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል በተዘጋጀው የምረቃት ስነ-ስርዓት ላይ የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ድኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ ተገኝተው በአስተላለፉት መልዕክት ባለሥልጣን መሥሪያቤቱ ያሠራው ብራንድ ተቋሙን በሚፈለገው ደረጃ ለመውሰድና ማህበረሰቡን የቁጥጥር ሥራ ባለቤት ለማድርግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል።
አክለውም ህብረተስቡ በጤና ግብዓቶች ቁጥጥር ላይ ጥቆማ በመስጠት ብቻ ሳይወሰን ባለሥልጣን መሥሪያቤቱ ለሚያወጣቸው የተለያዩ መመሪያዎች እንዲገዛ በማድረግ እንዲሁም የተቋሙን አዲስ ገፅታ በማስተዋወቅና በመገንባት ረገድ ብራንዲንጉ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት ሄራን ገርባ ፕሮግራሙን ሲከፍቱ በበኩላቸው እንደተናገሩት የተቋሙን ብራንድ ማሠራት ያስፈለገበት ዋና ዓላማ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በአዋጅ የተሰጠውን ኃላፊነትና ስያሜ የሚመጥን፤ የተቋሙን ገላጭ ምስልና ማንነት በመቅረጽ ተቋሙን በህብረተሰቡ ህሊናና ልብ ውስጥ ለማስቀረት ነው።
ብራንድ አሠርቶ በዛሬው ዕለት ይፋ ማድረጉን የገለጹት ወ/ሪት ሄራን አዲሱ ብራንድ ተቁሙ ወደ ፊት በግብዓቶች ቁጥጥርና የህብረተሰብን ጤና በመጠበቅ ረገድ የአፍሪካ የልህቀት ማዕከል የመሆን ራዕዩን እውን ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።
በመጨረሻም ብራንዲንጉን ከመቅርጽ አንስቶ ሥራውን በሐሳብ፣ በዕውቀት፣ በገንዝብ ለደገፉ፣ በሥራው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳትፎና ድጋፍ ላደረጉ አካላት የምስጋና ሰርተፍኬት ከዶ/ር ደረጄና ከወ/ሪት ሄራን እጅ ተበርክቶላቸዋል።