እያደገ ከመጣው የጤና ተቋም አገልግሎት ጋር በተያያዘ የማስተዋወቅ ተግባር በማናቸውም መንገድ የሚተላለፍበት ሁኔታ ደረጃውን ባልጠበቀ የጤና አገልግሎት እንዲሁም ሙያዊ ስነ ምግባርን ባላከበረ ማስተዋወቅ ምክንያት ሊደርስ የሚችለውን የጤና ችግር መግታት አስፈላጊ በመሆኑ፤ የጤና ተቋም አገልግሎት ማስታወቂያ ከመተላለፉ ወይም በሌላ የማሰተዋወቂያ ማስተላለፊያ መንገድ ከመተዋወቁ አስቀድሞ ዘርፉ የሚመራበትን ህግና ስርዓት መወሰን አስፈላጊ በመሆኑ፤ የጤና ተቋም አገልግሎት ማስታወቂያ በሚተዋወቅበት ጊዜ የህክምና ስነ-ምግባር፣ የህብረተሰቡን ባህል፣ እውቀት እና ልምድ ከግንዛቤ ያስገባ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፤ የጤና ተቋም አገልግሎት አሰጣጥ ማስተዋወቅ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ እንዲመራ ማስቻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒት እና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 661/2ዐዐ2 አንቀጽ 50(1) እና 55 (3) በተሰጠው ስልጣን መሠረት ይህን መመሪያ አውጥቷል፡፡