በአሁኑ ወቅት ከኮሮና ቫይረስ _ 19 በሽታ መከሰት ጋር ተያይዞ የተለያዩ ሀገራትና ብዙኃን መገናኛ የፊት መሸፈኛ ጭንብሎችን አስመልክቶ የተለያዩ መረጃዎችን እያወጡ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ተከትሎ በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ _ 19 በሽታ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ዜጎች የተለያዩ የፊት መሸፈኛ ጭንብሎችን ሲጠቀሙ ይታያል፡፡ ይሁን እንጂ ከበሽታው አደገኛነት ጋር ተያይዞ ስለምንጠቀምባቸው የፊት መሸፈኛ ጭንብሎች ምንነት፣ ከምን እንደተሠሩ፣ የት እንደተሠሩ፣ አግባብ ያለው የመንግስት አካል ዕውቅና እንደሰጠው ማረጋገጥ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የፊት መሸፈኛ ጭንብል መጠቀም ብቻ በቫይረሱ ከመያዝም ሆነ ከማስተላለፍ ሙሉ በሙሉ ስለማይከላከል ሌሎቹን የመከላከያ መንገዶች ማለትም እጅን ቶሎ ቶሎ በአግባቡ መታጠብ፣ አልኮል ያለው ሳኒታይዘር መጠቀም፣ አካላዊ ርቀት መጠበቅና ባለመጨባበጥ መከላከል ይቻላል፡፡
የተለያዩ የፊት መሸፈኛ ጭንብሎች በገበያ ላይ የሚገኙ ሲሆን የኮሮና ቫይረስ _ 19 በሽታን የመከላከል አቅማቸው ግን በሚሠሩበት የጥሬ ዕቃ፣ አዘገጃጀትና አጠቃቀም ይወሰናል፡፡
የፊት መሸፈኛ ጭምብሎች ዓይነቶች፦
- ከጨርቅ የተሠራ የፊት መሸፈኛ ጭንብል (ማስክ)(cloth masks)፦ በቤት ውስጥና በፋብሪካ ከመቶ ፐርሰንት(100%) ጥጥ ወይንም ተመጣጣኝ ደረጃ ካላቸው የጨርቅ ዓይነቶች የሚመረቱ የፊት መሸፈኛ ጭምብሎች ለሕክምና አገልግሎት ከሚውሉ የፊት መሸፈኛ ጭንብሎች የማይመደቡ ሲሆን የት እና ማን እነዚህን ዓይነት ጭንብሎችን ይጠቀም የሚለውን የጤና ሚኒስቴር የሚሰጠውን መግለጫና መመሪያ መከተል ያስፈልጋል ፡፡
- ለሕክምና አገልግሎት የሚውል የፊት መሸፈኛ ጭንብል (Medical mask):- ይህ ዓይነቱ የፊት መሸፈኛ ጭንብል ከሕክምና የፊት መሸፈኛ ጭንብሎች የሚመደብ ሲሆን ጭንብሉን ከለበሰ ታማሚ ሰው አፍ የሚወጡ ከፍ ከፍ ያሉ ቅንጣቶችን (large particles) አካባቢን እንዳይበክል ያግዛል፡፡ እንዲሁም ከፍ ከፍ ካሉ የደምና የሰውነት ፈሳሽ ፊዚካል ባሪዬር (physical barrier) በመሆን የጠብታ ብናኝ (droplets) አካባቢን እንዳይበክል ይከላከላል፡፡ በመሆኑም እነዚህን ዓይነት ጭንብሎችን መጠቀም የሚመከር ሲሆን ነገር ግን በዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እጥረት ስላለ ቅድሚያ የጤና ባለሙያዎች እንዲጠቀሙ ዕድሉን ብንሰጣቸው ጥሩ ነው፡፡ የእነዚህን ጭንብሎች ደህንነትና ጥራት የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ፈቃድና ዕውቅና የሚሰጣቸው ሲሆን በሕጋዊ አምራች የተመረቱ ወይንም በሕጋዊ አስምጪ ወደ ሀገር ስለመግባታችው ይህንን በመጫን https://eris.efda.gov.et/public/temporary_coc ማረጋገጥና መጠቀም ይኖርብዎታል ፡፡
- N95 የመተንፈሻ የሕክምና ጭንብል (Surgical N95 respirator):- ይህ ዓይነቱ የፊት መሸፈኛ ጭንብል ከሕክምና የፊት መሸፈኛ ጭንብሎች የሚመደብ ሲሆን የመደበኛ የሕክምና ጭንብልና የN95 መተንፈሻ ጭንብልን ጥምር ጥቅም ያለው ሲሆን በአካላዊ ከለላ (physical barrier) ከደምና የተለያዩ የሰውነት ጥቃቅን የጠብታ ብናኞችን በሳል ከአፍ የሚወጡትን እርጥበት ጨምሮ መከለካላል የሚያስችል ሲሆን በበሽታው የተጠቁ ታካሚዎችን የሚንከባከቡ የጤና ባለሙያዎች ብቻ እንዲጠቀሙበት ይመከራል፡፡ የእነዚህን ጭንብሎች ደህንነትና ጥራት የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ፈቃድና ዕውቅና የሚሰጣቸው ሲሆን በሕጋዊ አምራች የተመረቱ ወይንም በሕጋዊ አስመጪ ወደ ሀገር ስለመግባታችው ይህንን በመጫን https://eris.efda.gov.et/public/temporary_coc ማረጋገጥና መጠቀም ይኖርበዎታል ፡፡